ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሶስት የጀርመን መንግስት የልማት ድርጅቶች ውህደት ፈጠሩ


በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሚስስ ሌዝሎር ሳይረስ በኤምባሲው ቅጥር ጊቢ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት መንግስታቸው የሁለቱን ሀገራት የጋራ ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከምንጊዜውም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ለሚካሄዱት የልማት ስራዎችም መንግስታቸው እየሰጠ ያለውን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የልማትና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩት ጂ ቲ ዜድ፣ ዲ ኢ ዲ እና ኢንወንት የተባሉ ሶስት ድርጅቶችም ውህደት በመፍጠር የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ጂ አይ ዜድ በሚል መሰየማቸውን አምባሳደሯ ተናግረዋል፡፡

የጂ አይ ዜድ ዳይሬክተር ሚስተር አልሪች ሞር በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ከመቶ ዓመት በላይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳለና የልማት ድጋፍ ማድረግ ከጀመሩም ከሃምሳ ዓመት በላይ እንዳስቆጠሩ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ጂ አይ ዜድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱት የልማት ስራዎች ወደ 31 ሚሊዮን ዩሮ መደገፉም ተገልጿል፡፡ --AddisAbabaCity

comments powered by Disqus
Bookmark and Share