የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት ማምሻውን ተጠናቀቀ
September 5th, 2012በታላቁ መሪ ጓድ አቶ መለስ ዜናዊ የህሊና ፀሎት መደበኛ ስራውን የጀመረው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ ጫፍ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ ዜና እረፍቱን ካሰማበት ዕለት ጀምሮ መሪር ሀዘኑን በመግለፅና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በየተሰማራበት ለውጤታማነት በመትጋት ለማስቀጠል ያሳየውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ የታላቁ መሪ ህልፈት ለሀገራችን፣ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ተራማጅ ኃይሎችና ጭቁን ህዝቦች ከፍተኛ ጉዳት መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የሀገራችን ህዳሴ መሀንዲስ የነበረው ታላቅ መሪ ድንገተኛ ህልፈት በፓርቲው፣ በመንግስትና በመላው ህዝባችን ዘንድ ለመቀበል የሚቸግር መራር እውነት መሆኑን የተመለከተው ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴው ህይወቱን ሙሉ የተዋደቀለት የኢትዮጵያ ህዳሴ በህይወት ዘመኑ በሰጠው በሳል አመራር ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ባደረጉ የገጠርና ከተማ ልማት ሥራዎች፣ በመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ በተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት መታየቱን ገምግሟል፡፡ በጓድ መለስ ዜናዊና በኢህአዴግ አመራር ከፍተኛ እድገት ማሳየት የጀመረው የሀገራችን ህዳሴና በዓለም አደባባይ ያላት ተሰሚነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለተግባራዊነቱም እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በጋራና በተናጠል በየተሰማራበት መስክ ሁሉ ለመረባረብ ያሳየው ቁርጠኝነት ለፓርቲውና ኢህአዴግ ለሚመራው መንግስት ከፍተኛ አቅም እንደሆነ በማውሳት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን አድናቆትና ምስጋና አቅርቧል፡፡
የታላቁ መሪና የኢህአዴግ ራዕይ በፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ተቀምሮ በገጠርና በከተማ ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተመንዝሮ በህዝቡ ሰፊ ተሳትፎ የሚሊዮኖችን ህይወት በፍጥነት ለመለወጥ በተደረገው ጥረት የፓርቲው አባላትና የመላው ህዝባችን ሀብት ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ ፓርቲው በዚህ ሂደት ውስጥ ከህዝቡ ጋር እየወደቀ እየተነሳ በተግባርም እየበቃ መምጣቱንና መላው የሀገራችን ህዝብ በመረሪር ሀዘንና በእንባው መሃል የገለፀው እና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የሚያስችለው ቁርጠኝነትም ይበልጥ እንዲተጋ እንዳነሳሳው ገምግሟል፡፡
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የህዝቡን መነሳሳት እና ለፓርቲው የሰጠውን አደራ ገምግሞ በታላቁ መሪ በሳል አመራር እና በኢህአዴግ የተነደፈውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በከፍተኛ ርብርብ ለማሳካት፣ የህዝቡን ተነሳሽነትም የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን በመደገፍ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር እና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በበለጠ ግለት ለማስቀጠል ወስኗል፡፡ በገጠር በተፋሰስ ልማት፣ በመስኖና በተለያዩ የውሃ አሰባሰብ ዘዴዎች እንዲሁም በዘመናዊ የግብአት አቅርቦትና የሙሉ ፓኬጅ አጠቃቀም ዙሪያ አርሶ አደሩን በማሳተፍና በመደገፍ የገጠር ልማት ሥራዎችንና የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ተጠቃሚነት በከፍተኛ ፍጥነት ለማስቀጠል አፅንኦት ሰጥቶ መክሯል፡፡ በከተሞች የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረውን የጥቃቅንና አነስተኛ ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ለማስፋት በመረባረብ፣ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸውን የባቡር፣ የኢንዱስትሪዎችና የታላቁን ህዳሴ ግድብ ጨምሮ ሌሎችም የኃይል ማመንጫ ተቋማት ግንባታዎችን በማስቀጠልና በተለይም መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል በህዝቡ በራሱ ተሳትፎ የህዝቡን አደራ በብቃት ለመወጣት በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ አፅንኦት ሰጥቶ መክሯል፡፡
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የመንግስትን የገቢ አቅም የማጠናከር፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንት የማበረታታት፣ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር፣ የኤክስፖርት ገቢያችንን የማሳደግ፣ ልማታዊ የግል ዘርፍን የማጐልበት ስራዎችን አፈፃፀም በተመለከተ እስካሁን ያሉትን ሁኔታዎች የቃኘ ሲሆን አሁን ካለው መነሳሳት አኳያ ዕቅዶችን በፌደራል እና በክልሎች በዝርዝር ፈትሾ ለላቀ ግብ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አመልክቷል፡፡
የህዝቡን ቁጭትና አደራ በህዝቡ በራሱ በተደራጀና ቀጣይነት ባለው ተሳትፎ ወደ ውጤት በመቀየር የተጀመረውን ፈጣን እድገትና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማስቀጠል የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ወደ ዝርዝር እቅድ ተቀይረው በመጪው የግንባሩ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዳብሮና ፀድቆ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ወስኗል፡፡
የባለ ራዕዩና ታላቁ መሪ የጓድ መለስ ዜናዊን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የተጓደለው አመራር በሚሰየምበት አቅጣጫ ዙሪያ የመከረ ሲሆን የአመራር ምደባ ጉዳይ ለጋራ ዓላማ በሚደረግ ትግል ውስጥ አንድን ጓድ ይበልጥ መስዋዕት ይከፍል ዘንድ ከመመደብ ያለፈ ትርጉም የሌለው ቀላል ጉዳይ መሆኑንና ዋናው ስራም ሁሉም በየተሰማራበት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት መሆኑን አውስቷል፡፡ በመሆኑም ዋናው ጉዳይ የሆነው ለህዝቡ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቂ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት አቅጣጫ ዝግጅት እየተደረገ የግንባሩን ሊቀመንበርና ም/ሊቀ መንበር የመሰየም ጉዳይ የግንባሩ ምክር ቤት ስልጣን በመሆኑ በመጪው መስከረም የመጀመሪያ ሳምንት በሚካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲፈፀም ወስኗል፡፡
በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ መሪያችን ህልፈት ወቅት ያሳየውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቀጣይም ድህነትን በፍጥነት በመናድ የህዝባችንን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሀገራችን ህዳሴ ለማፋጠን በሚያደርገው ርብርብ ከጎኑ እንዲቆም ግንባሩ ጥሪውን በማስተላለፍ ስብሰባውን አጠቋል:: --EPRDF