ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ባጋጠማቸው የጤና መታወክ በውጭ ሀገር ሕክምና በመከታተል ላይ ናቸው


የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ባጋጠማቸው የጤና መታወክ በውጭ ሀገር ሕክምና በመከታተል መሆናቸውንና በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ገለጹ፡፡ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ በረከት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጤንነት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የጤና መታወክ ያጋጠማቸው ቢሆንም አስፈላጊው ህክምና በውጭ አገር በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የህክምና እርዳታ ተደርጓላቸው በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙና በቅርቡም ሥራቸውን እንደሚጀምሩ አቶ በረከት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለረጅም ጊዜያት በመንግስትና በአገራዊ ኃላፊነቶች ያለ ዕረፍት ሲሰሩ በመቆየታቸው የጤና መታወክ እንዳጋጠማቸው የህክምና ክትትል የሚያደርጉላቸው ሀኪሞች ማስረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የህክምና ክትትል ባደረጉላቸው ሀኪሞች ዕረፍት እንዲያደርጉ በመወሰኑ በአሁኑ ወቅት በህክምና እረፍት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የህክምና እረፍታቸውን እንዳጠናቀቁ የመደበኛ ስራቸውን እንደሚጀምሩም አቶ በረከት አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤና መታወክ ተከትሎ በመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መካከል የስልጣን ሽኩቻ አለ የሚባለው ጉዳይ ትክክል ነወይ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሰላቸው ጥያቄ አቶ በረከት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ወሬው መሰረተ ቢስና በኢህአዲግ የፖለቲካ ባህል ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች በህግ የተደነገገ ሥልጣን መሠረት በማድረግ ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ በመሆኑ ሃገራዊ ስጋት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወናቸው ስኬታማ ተግባር ተከናውኗል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በከተሞች ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የባቡር ፣ የስኳር እና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያልተገኙባቸው 19ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት የ2005 ረቂቅ በጀት በስኬት መጠናቀቁን አቶ በረከት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ብሔራዊ ደህንነቷን በማስከበር ላይ እንደምትገኝም አስታውቀዋል፡፡ --ENA

comments powered by Disqus
Bookmark and Share