የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከፍተኛ የአመራር ሰጪ የነበሩት ዶክተር እሌኒ ሊተኩ ነው
June 22nd, 2012የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአደረገው የአመራር ሽግግር የምርት ገበያው መስራችና ከፍተኛ አመራር ሰጪ የነበሩት ዶክተር ዕሌኒ ገብረ መድኅን የአመራር ሰጪነታቸው ቦታ በሌላ እንደሚተካ ዛሬ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ዕሌኒ ገብረ መድኅን ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የአመራር ሽግግሩ የተደረገው ባለፈው ግንቦት 2002 ዓ.ም ተቀጥረው በነበሩ በዓለም አቀፍ የሥራ አመራር ባለሙያዎች ስብስብ ታቅዶ ተግባራዊ በሆነው ውጤታማ የሽግግር አተገባባር ነው።
በተያዘው ዕቅድ መሰረት ቀጣይ የአመራር ኃላፊነት ርክክብ የሚደረገው ከሚቀጥለው ሐምሌ 2004 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል። ለምርት ገበያው እድገት በቀጣይም በአማካሪነት ከአመራር ቦርዱ ጋር አብረው እንደሚሰሩና ድጋፋቸውን እንደማያቋርጡ ዶክተር ዕሌኒ ተናግረዋል ። ስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የተማሩት ዶክተር ዕሌኒ በዓለም ባንክ ከፍተኛ የሴክተር ኢኮኖሚስት ሆነውም አገልግለዋል።
በቀጣይ አቶ አንተነህ አሰፋ የወቅቱ የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከሐምሌ 25 ቀን 2004 ጀምሮ ተተኪ የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በምርት ገበያ የአመራር ቦርድ መሾማቸውንም ዶክተር ዕሌኒ ተናግረዋል። አቶ አንተነህ አሰፋ በአመራር ችሎታቸው በፋይናንስ ዘርፍ ከ15 ዓመታት በላይ ባካበቱት የሥራ ልምድ የቀረቡትን መስፈርቶች ሊያሟሉ በመቻላቸውና ለምርጫው ከተወዳደሩት ዕጩዎች በልጠው በመገኘታቸው ሊሾሙ መቻላቸውን አመልክተዋል። --ENA